በ” KOREE NAGEENYAA -የደህንነት ኮሚቴ” በሚል ስም በመንግስት የሚደገፉ ወንጀሎችን ስለፈጸሙ አካላት ተጠያቂነት
የኦነግ መግለጫ
በአውሮፓ ኣቆጣጠር ፌብሩዋሪ 23፣ 2024 ሮይተርስ (REUTERS) በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በንጹሃን የኦሮሚያ ዜጎች ላይ የፈጸሙትን እጅግ ዘግናኝ የሆነ የምርመራ ውጤት ይፋ አድርጓል። እነዚህን ግፍ ለዓመታት በተከታታይ ብንዘግብም፣ የአለም ማህበረሰብ ምላሽ በጣም አናሳ ነው ወይም ምንም ምላሽ የለም። የዜና ዘገባው “በኢትዮጵያ ትልቁ እና በሕዝብ ብዛት በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ ሚስጥራዊ ኮሚቴ የተካሄደውን ሽምቅ ውጊያ ለመደምሰስ ከህግ አግባብ ዉጭ ግድያ ፈጽሟል እና በህገወጥ የእስራት ትእዛዝ አስተላልፏል” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል1።
የዚህን ስውር ኮሚቴ ማንነት እና ተግባር በጥልቀት ስንመረምር፣ REUTERS እንዳስታወቀው “ Koree Nageenyaa -ኮሬ ኔገኛ” የተባለው ሚስጥራዊ ቡድን በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ስራውን መጀመሩን አስታውቋል። ኮሚቴው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ጦርነት ለመመከት አብይ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ በሚል የተመሰረተ ነው። ስለ ኮሬ ናጌኛ ስብስብ የበለጠ ግንዛቤ ለመስጠት፣ በአብይ ብልፅግና ፓርቲ የሚመራ ሆኖ የኦሮሚያ ክልል ፅህፈት ቤቶች እንደተካተቱበት እና በአብይ የቀድሞ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የአሁኑ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመሩ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል።በተለይ አቶ ሽመልስና ሌሎች የኮሚቴ አባላት ኦሮሞዎች መሆናቸው ይታወቃል። በኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ መሪ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ የኦሮሚያ የጸጥታ ኃላፊ አቶ አራርሳ መርዳሳ እና ሌሎች በርካታ የፖለቲካና የጸጥታ ኃላፊዎችም የዚህ ቡድን አካል መሆናቸውን በዘገባው የተጠቀሱ ምንጮች ጠቁመዋል። እነዚህ የጸጥታና የፓርቲ መዋቅሮች እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመቀናጀት እነዚህን እኩይ ተግባራት በንፁሃን ዜጎች ላይ ይፈፅማሉ። ለምሳሌ በዞን ደረጃ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን የሚቆጣጠሩ ኃላፊዎች “የኮሬ ናጌኛ” የተዘረጋ ክንድ ወይም መዋቅር ሆነው ያገለግላሉ።እነዝህም፡
1. የዞን አስተዳደር ኃላፊ
2. የዞኑ አስተዳደር ምክትል ኃላፊ
3. የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ
4. የብልጽግና ፓርቲ የዞን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
5. የዞን ፖሊስ ኃላፊ
6. በዞን ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት አዛዥ።
የኮሬ ናጌኛ አጀማመር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጭነት መጀመሩንም ዘገባው አረጋግጧል። ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ኮሚቴው የተቋቋመው በአብይ አነሳሽነት እንደሆነ ይገልፃል። በ2022 መጀመሪያ ላይ ስለኮሚቴው እንቅስቃሴ ቢያንስ አንድ ጊዜ ለአብይ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ጊዜ በባለሥልጣናት እና በካሬዩ ሽማግሌዎች በተለይም በካሬዩ ሽማግሌዎች ግድያ ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ሲል ዘገባው አክሎ ገልጿል። በኦሮሚያ በተካሄደው የምርመራ ዘገባ የካራዩ ጋዳ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ግድያ በመንግስት የጸጥታ አባላት መፈጸሙን አረጋግጧል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ማንም ተጠያቂ አልተደረገም፡፡
በኮሬ ናጌኛ ከተፈፀሙት ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ግድያዎች መካከል እ.ኤ.አ. በ2021 በኦሮሚያ በ14 የጋዳ አመራሮች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ መንግስት ቀደም ሲል በኦነስ (OLA) ተዋጊዎች ላይ ያላከከ መሆኑንም ግኝቱ ይፋ አድርጓል። ኢሰመኮ ቀደም ሲል ባደረገው ምርመራ የጸጥታ አካላት ግድያውን መፈጸማቸውንም ዘገባው አመልክቷል። ጉዳዩን የሚያውቁ ሁለት የኢሰመኮ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፣ ግድያ እንዲፈፀም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ትዕዛዝ መስጠታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና እማኞች ገልጸዋል።
በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው፣ የኮሬ ናጌኛ ከሚባሉት አስደንጋጭ ባህሪያት አንዱ እጅግ በጣም ሚስጥራዊነቱ ነው። የጸጥታ ኮሚቴው ጥብቅ ከሆነው ኦፊሴላዊ ክባብ በዘለለ ብዙም አይታወቅም። በሳምንት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ጠንካራ የደህንነት እርምጃዎችን በመዉሰድ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ በስብሰባ ጊዜ ሕንፃው ከሌሎች ሰራተኞች ባዶ ተደርገዋል፣ ታዳሚዎች ስልኮቻቸውን ያስረክባሉ እና በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ መጨረሻ ላይ ሰነዶች ይሰበሰቡ ነበር። የንፁሀን ግለሰቦች እጣ ፈንታ በእነዚሁ ኮሚቴ አባላት እጅ ነው ፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ ዳኛ ኮሬ ነጌኛ አንድ ሰው መታሰር እንዳለበት ትዛዝ አስተላልፈዋል ብለዋል ። ከዚያም ያለፍርድ ቤት ማዘዣ፣ ምርመራ እና የፍትህ ሂደት ያንን ሰው መያዛቸዉንም ዳኛው ተናግሯል።
በተጨማሪም ኮሬ ናጌኛ በታዋቂው ኦሮሞ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ግድያ እና እስራት ፈጽሟል ሲል ዘገባው አመልክቷል። እ.ኤ.አ ሰኔ 2020 መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በከሰሰበት ግድያ ታዋቂው የኦሮምኛ ዘፋኝ Haacaaluu Hundeessaa በተገደለበት ወቅት በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ 200 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን እና 5,000 ሰዎች መታሰራቸውን ዘገባው በትክክል አጋልጧል የሰባአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች.እንዳረጋገጡት፡፡ የኦሮሚያ ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከ19ኙ የክልሉ ትላልቅ ከተሞች እና 21 ዞኖች ጋር ተከታታይ የስካይፐ ጥሪ መምራታቸውን የኮሬ ናጌኛ አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ የተሳተፉት ሁለቱ ሰዎች ተናግረዋል። እነዚህ ሁለት ምስክሮች እንዳሉት ሽመልስ እና ፍቃዱ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች እንዲታሰሩ እና ሌሎች እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥተዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ እንደገለፀው ሽመልስ ሰልፉ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ አንዱን የዞን አስተዳዳሪ ጠራቸውና አዘው ሰልፈኞች ላይ እንዲተኩሱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ሲል ከእነዚህ የኮሬ ናጌኛ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ተናግሯል።
የ ሮይተርስ (REUTERS) ዘገባ ሁሉንም ታማኝ ምንጮች ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እና እጅግ ጠንካራ ዘዴዎችን በመጠቀም ጥልቅ ጥናት ላይ ተመሰረተ ዘገባ ነው። ከ30 በላይ የፌዴራል እና የአካባቢ ባለስልጣናትን፣ ዳኞችን፣ ጠበቆችን እና በባለስልጣናት በደል ሰለባዎችን አነጋግሯል። በተጨማሪም፣ ሮይተርስ (REUTERS) በአካባቢው የፖለቲካ እና የፍትህ ባለስልጣናት የተዘጋጁ ሰነዶችን ገምግሟል፡፡ እነዚህ ቃለ-መጠይቆች እና ሰነዶች ስለ ኮሬ ነጌኛ (Koree Nageenyaa) አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ብርሃን ፈንጥቀዋል። ከዚህ በላይ በኮሚቴው ስብሰባ ላይ የተሳተፉትን ሚልኬሳ ሚdhaግሳ ጨምሮ ቀደም ሲል በፓርቲው አመራርነት በነበራቸው አቋም ምክንያት የመጀመሪያ መረጃ ያላቸውን ግለሰቦች አነጋግሯል። በተጨማሪም ሮይተርስ (REUTERS) የምርመራ ውጤቱን ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኃላፊ ለአቶ ዳንኤል በቀለ አቅርቧል፡ የኮሬ ነጌኛ ን መኖር በማመን፣ “ከህግ አግባብ ውጪ የግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ ማሰቃየት እና ዝርፊያ በርካታ ጉዳዮችን መዝግበናል ” በማለት ተናግሯል።
በሪፖርቱ እና ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከገለጽናቸው እኩይ እና አስከፊ የመብት ፣የማስፈራራት ፣የመሰወር፥ የማሰቃየት እና ከህግ አግባብ ዉጭ ግድያ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙት በመደበኛ የተደራጁ የመንግስት መዋቅሮች – ኮሬ ናጌኛ ተብሎ በተሰየመ ኮሚቴ እና ጥላ ስር የሚፈጸሙ መሆናቸው ነው። እስከ ዞን፣ ወረዳ፣ ከተማ እና ቀበሌ አስተዳደሮች ድረስ የተዘረጋ መዋቅር ነው። ይህ የእብደት ዓላማ ባለው አስተሳሰብ የሚመራ እና ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ በማይችሉ ንቃተ ህሊና እና በግልፅ በተዘጋጁ እቅዶች የሚከናወን ነው። አሁን ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀው ግን በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ዞኖች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ዉጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ ስቃይ እና ምዝበራ ዛሬም በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጥሏል። እነዚህ አስደንጋጭ አረመኔያዊ ድርጊቶች በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን በቂ ምላሽ እየተሰጣቸው አይደለም። የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ሰላም ወዳድ አለም አቀፍ ማህበረሰቦች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘግናኝ ግዲያዎች እንዲቆሙና እነዚህ ቡድኖች ለፈጸሙት አሰቃቂ ተግባር ተጠያቂዎች እንዲሆኑ በአጽንዖት ግፊት ኣንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
ድል ለሰፊው ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻ ግንባር (ኦነግ)
መጋቢት 11 ቀን 2024 ዓ.ም