ከ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ
እንደሚታወቀው በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አያያዝ ቅሬታ ያለን አስር የምንሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ መሥርተን በመንቀሳቀስ አሁን ላይ ወደ አስራ አምስት መድረሳችን የሚታወቅ ነው። በሂደቱ ላይ ከሌሎች ጋር ያለን ልዩነት በተደጋጋሚ የገለፅን ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ ልዩነቶች እንዲፈቱና በሁለንተናዊነት አብረን ለሀገራችን ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት የምክክር ኮሚሽኑ አመራር በተለይ ዮናስ አዳዬ በ21/06/2015 ለኢዜአ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ከሁሉም ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም በሂደቱ ቅሬታ የነበራቸው ጋር መተማመን ላይ ደርሰናል” ማለታቸውን አይተናል።
ይሁንና የምክትል ኮሚሽነሩ መግለጫ ከእውነት የራቀ ከመሆኑም ባሻገር ድፍረት የተሞላበት እንዲሁም ከአሁን በፊትም በሪፖርተር ጋዜጣና በአሜኮ ቀርበው አሳሳች መረጃ የሰጡ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን። ይሁንና ይህ የግለሰቡ የፈጠራ ሐሳብ እንጂ በኮሚሽን ደረጃ የሌለ አቋም መሆኑን፣ በመሆኑም ዜናውንም ከገፁ ማስነሳታቸውና በግልፅ ድርጊቱን ባያስተባብሉም የተባለው ነገር እውነት አለመሆኑን ጠቅሰው ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ ለማድረግ ሞክሯል ለዚህም አድናቆት አለን።
ይሁንና ፡
1/ ኮሚሽኑ መግለጫውን በመሸፋፈን ሳይሆን በይፋ እንዲያስተባብልና ለተጀመሩ ምክክሮች ራሱ መልሶ እንቅፋት እንዳይሆን እናሳስባለን። በግለሰቡም ላይ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀፅ 15 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ።
2/ በኮከሱ በኩል ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ውጤት እስኪያመጡም ድረስ የምንቀጥልበት ይሆናል። ሆኖም ግን በተለይ ከኮሚሽኑ ጋር ተገናኝተን የማናውቅ ሲሆን የነበሩን የልዩነት ነጥቦች አሁንም እንዳሉ መሆናቸውና የተቀየረ ነገር አለመኖሩን ለአባላቶቻችን፣ ለደጋፊዎቻችንና ለመላው ህዝባችን ለማሳወቅ እንወዳለን። 3/ እነዚህ ጉዳዮች ግልፅ እስኪሆኑና አሳማኝ ምክንያት እስኪቀርብባቸው ድረስ ኮከሱ ትግሉን የሚቀጥልና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ውይይቶች ለፍሬ እስኪበቁ ድረስ ለውጥ እንደማይኖር ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም እውነቱን ተረድተው ኮከሱን እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
23/06/2015
አዲስ አበባ